የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ.ር) የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃና መንገድ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ጎንደርና አካባቢው እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡ በዚህ መነሻነትም ከውሃና ኢነርጂ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም መንገድ ሚኒስትሮችና ባለድርሻዎች ጋር ባደረጉት ግምገማ፤ በቅርብ ለምርቃት የበቃው የአባይ ግድብ እና ስራው በጥራት እየተጠናቀቀ የሚገኘው የጎርጎራ ፕሮጀክት በክልሉ ስኬታማ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን አመላካቾች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ የመገጭ ግድብ እና ከአዘዞ – አየር መንገድ ሊሰራ የነበረው 11 ኪ/ሜ መንገድ በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜና ጥራት ባለመጠናቀቃቸው በህዝብ ዘንድ ምሬትን መፍጠራቸውን ገልጸው፤ ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውላቸው ተሰርዞ ለአዲስ ኮንትራት እንዲሰጡ መመሪያ ሰጥተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በግምገማ መድረኩ እንደተገለጸው ለ4 ጊዜ ያህል የስራ ኮንትራቱ እንደ አዲስ ውል እየተያዘ በአጠቃላይ 6.4 ቢሊዮን ገንዘብ ወጪ ተደርጎበት እየተሰራ የነበረው የመገጭ ሰራባ ፕሮጀክት በ2001 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም በመፈጸም አቅም፣ በማህበራዊ፣ በቴክኒካል፣ በፋይናንስና መሰል የአቅም ችግሮች ሳቢያ ሳይጠናቀቀ ድፍን 10 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ በማህበረሰቡም ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) እንደተናገሩት፤ የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ከክልሉ መንግስት ጋር በትብብር በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ከተማው ውስጥ ኮሌጅ አካባቢ፣ አንገረብ ግድብ በታችና ቆላ ድባ ላይ በአጠቃላይ 40 ሊትር ውሃ በሰከንድ ማምረት የሚችሉ 3 ጉድጓዶች እንደተቆፈሩ እና 2 ተጨማሪ ጉድጓዶች በዕቅድ እንደተያዙ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ ጉድጓዶቹ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የመገጭ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ የነዋሪውን የመጠት ውሃ ጥያቄ በመፍታት ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ የመገጭ ግድብ ከፍተኛ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ፈሶበት ፍሬ አልባ ስለሆነ፤ ስራውን ይሰራ የነበረው ኩባንያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮንትራቱን እንዲሰርዝና መስራት ለሚችል አዲስ ኩባንያ ውል በመፈራረም ስራው በአዲስ መልክ እንዲጀመር ነው ያስገነዘቡት፡፡ አዲስ የሚሰራውን ግድብም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አፈጻጸሙን በመከታተል፣ ክፍተት በመሙላትና የሚለካ ውጤት በማሳየት የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መቀረፍ ይኖርበታ፤ መንግስትና የፋይናንስ ሚኒስቴርም በቅርበት ክትትል የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የተቆፈሩ 3 የውኃ ጉድጓዶች በጥቂት ወራት ውስጥ መስመር ተዘርግቶላቸው ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ መፍጠር ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡